በአሶሳ ዞን ማረሚያ ቤቶች መምሪያ ለሚገኙ የህግ ታራሚዎች የንባብ አገልግሎት የሚሰጥ ቤተ-መፅሐፍት ቤት ሥራ መጀመሩ ተገለፀ፤

ጥቅምት 30 / 2012 ዓ.ም (አሶሳ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት የማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን በአሶሳ ዞን ማረሚያ ቤቶች መምሪያ ለሚገኙ የህግ ታራሚዎች መፅሐፍ ለተራበ አዕምሮ ከተባለ በጎ አድራጊ ድርጅት እና ከአሶሳ ዩንቨርስቲ ጋር በመተባበር በተገኘ ድጋፍ ቤተመፅሐፍት ቤት መቋቋሙን የዞኑ ማረሚያ ቤቶች መምሪያ ኃላፊ ኮ/ር ሀሩን አብዱረሂም ገልፀዋል፡፡
መጽሐፍት ዓለም ሁሉ የቀየሩ የስልጣኔ ዋና ቁልፎች ናቸው። ዓለም እዚህ የደረሰችው መፃሕፍት ታትመው ነው። የሰው ልጅ የዕውቀት ብልፅግና፣ ልዕልና፣ ሃያልነት፣ ግርማ ሞገሱ ሁሉ ከመፃሕፍት ጋር የተቆራኘ ነው። መፃሕፍት የሌለውና የማያነብ ሰው ባዶ ቤት ውስጥ፣ ምንም ነገር በሌለበት ብቻውን እንደሚኖር ፍጡር ይቆጠራል። የሚያናግረው ሰው እንደሌለው፣ የሚያየው፣ የሚያልመው ሃሳብ እንደሌለው ፍጡር ይቆጠራል። ማንበብ የሰው ልጅ መሆንን ይጠይቃል። ሰው ፣ ሰው ለመሆን ማንበብ አለበት። ካለበለዚያ ብዙ ነገሮችን ከሌሎች እንሰሳት ጋር ይጋራል። የሰው ባህሪያትን ያጣል።
የዓለም የሥልጣኔ አውራ ከነበሩት አገራት መካከል አንዷ የነበረችው ሐገራችን ኢትዮጵያ ዛሬ የሥልጣኔ አውራ ሆናለች። የዚህ ምክንያቱ ሌላ አይደለም። የዕውቀት ማነስ፣ ያለማንበብ ችግር የፈጠረብን አበሳ ነው። ሌላው ዓለም የበለጠን በማንበቡ ነው። ንባብ የሕይወት መሠረት ነው። ያሉት ለአሶሳ ዞን ማረሚያ ቤቶች መምሪያ ለተቋቋመው ቤተ-መፅሐፍት ቤት ድጋፍ ያደረጉት ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ እና ደራሲ ሠላማዊት በለጠ ናቸው፡፡

የአሶሳ ዩንቨርስቲ ፕረዝዳንት ዶ/ር ከማል አብዱረሂም በፕሮግራሙ ላይ ባለረጉት ንግግራቸው “ማንበብ ትልቅ ሀብትን ያጎናፅፋል። እስከዛሬ በአለማችን ላይ ስለተከሠቱ እና በሌሎች ሰዎች ስለተሰሩ ነገሮች በሙሉ ማወቅ የምንችለው ማንበብ ስንጀምር ነው።” እናም በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በህግ ጥላ ሥር የሚገኙ የህግ ታራሚዎች ከማረምና ማነፅ ጎን ለጎን በማረሚያ ቤቱ ውስጥ የተከፈተው የቤተ-መፅሐፍት ቤት ታራሚዎች በማረሚያ ቤቱ ቆይታቸው ዕውቀታቸውን ከማዳበር እንደሚያስችልና ወደፊትም ዩንቨርስቲው ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ዳግም ቃል

ገብተዋል፡፡
መረጃውን ያደረሰን፡- የክልሉ ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮ/ር አልቃሱም አወድ ነው፡፡