የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ይቅርታ ቦርድ በልዩ ሁኔታ ይቅርታ ለመስጠት የሚያስችለዉን መመሪያ ቁጥር 1/2017 ዓ.ም መሠረት በማድረግ ይቅርታ በሚሰጣቸዉ ታራሚዎች ዙሪያ ተወያየ።
(አሶሳ፤ መጋቢት 05/2017ዓ/ም) የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግስት ይቅርታ ቦርድ በልዩ ሁኔታ ይቅርታ ለመስጠት የሚያስችለዉን መመሪያ ቁጥር 1/2017 ዓ.ም መሠረት በማድረግ ይቅርታ በሚሰጣቸዉ ታራሚዎች ዙሪያ የክልሉ ፍትህ ቢሮ ኃላፊና የቦርዱ ሰብሳቢ አቶ መሀመድ ሀሚድ በመሩት መድረክ ዉይይት ተደርጎ የዉሳኔ ሀሳብ ተሰጥቷል።
በክልሉ የይቅርታ አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 134/2008 ዓ/ም እና የይቅርታ አሰጣጥ ሥነ-ሥርዓት ደንብ ቁጥር 143/2012 ዓ.ም ላይ የተሰጡት ትርጉሞች በልዩ መመሪያዉም ተፈፃሚነት እንደሚኖራቸዉ የቦርዱ ሰብሳቢ አስታዉሰዉ የይቅርታ ዓላማም ከክልሉ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር ይቅርታ መሰጠቱ ያለው ማኅበራዊ ፣ፖለቲካዊና፣ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳን ለማሳካት በልዩ ሁኔታ ይቅርታ መስጠት፤ በማረሚያ ቤቶች ያለውን መጨናነቅ በመቀነስ የዜጎችን ሰብአዊ መብት ማስከበርና የታረሙ እና የታነፁ ታራሚዎች ወደ ኅብረተሰቡ ተቀላቅለው አምራች ዜጋ እንዲሆኑ ማድረግ እና ታራሚዎች መንግስት ይቅር ባይ መሆኑን ተገንዝበዉ የልማቱ አካል በመሆን ራሳቸዉንና ቤተሰቦቻቸዉን መደገፍ እንድችሉ ማስቻል መሆኑን ገልፀዋል።
በክልሉ ፍትህ ቢሮ የህግ አገልግሎት ዘርፍ ም/ቢሮ ሀላፊ በአቶ አማር ረጀብ የሚመራዉ የቦርዱ ቴክኒክ ኮሚቴ በክልሉ በሶስቱም ማረሚያ ቤቶች ተዘዋዉሮ የይቅርታ መስፈርቱን ያሟላሉ ብሎ ያመነባቸዉን የይቅርታ ተጠቃሚዎች ዝርዝር መረጃ ለቦርዱ አቅርቧል።
የክልሉ ይቅርታ ቦርድ አባላትም የቀረበዉ የይቅርታ ጥያቄ የይቅርታ አዋጁን እና አዋጁን ለማስፈፀም የወጣዉን ደንብ ያከበረ መሆኑን በጥልቀት መርምሮ የመንግስትንና የህዝብን ጥቅም ባስከበረ መልኩ የይቅርታ ጥያቄዉ ተፈፃሚ ሊሆን እንደሚገባ ሀሳብ አስተያየት ቀርቦ የጋራ ሶምምነት ላይ ተደርሶ ቦርዱ ይቅርታ ሊደረግላቸዉ ይገባል ያላቸዉን የህግ ታራሚዎች በመምረጥና በመለየት ይቅርታ እንድደረግላቸዉ የዉሳኔ ሀሳብ የሰጠ መሆኑን እየገለፅን የዉሳኔ ሀሳቡ በክልሉ መንግስት ሲፀድቅ ይቅርታ የተደረገላቸዉን አካላት መረጃ ተደራሽ የምናደርግ መሆኑን እናሳዉቃለን።

