የክልል ማረሚያ ቤት ኮሚሽኖች ከክልል ጤና ቢሮዎች ጋር በቅንጅት ሊሰሩ ይገባል ተባለ።
አዳማ-ሚያዚያ 23/2017 ዓ.ም (የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን)
ለተከታታይ 3 ቀናት በአዳማ ከተማ ሲካሄድ የቆዬው የማረሚያ ቤቶችን የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ለማሻሻል የሚያስችል የምክክር መድረክ ተጠናቋል።
የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን እና የጤና ሚኒስቴር በመተባበር ባዘጋጁት የጋራ የውይይት መድረክ ላይ የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል የኑስ ሙሉ ባስተላለፉት መልዕክት ታራሚዎች በማረሚያ ቤት የእርምት ቆይታቸው የጤና አገልግሎት የማግኘት መሰረታዊ መብት መሆኑን ተናግረው የተሻለ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ማረሚያ ቤቶቻችን ከየአካባቢያቸው ካሉ የጤና ተቋማት ጋር በቅንጅት መስራት ይጠበቃል ብለዋል።
በዚህም በሁሉም ክልሎች የሚገኙ የማረሚያ ኮሚሽኖች ከክልል ጤና ቢሮዎች ጋር ጥብቅ ቁርኝት በመፍጠር የህግ ታራሚዎች ከበሽታ መከላከል እስከ ህክምና አገልግሎት ድረስ በአግባቡ የጤና ተጠቃሚ እንዲሆኑ መሰራት አለበት ብለዋል፡፡
ኮሚሽኑ የማረም ማነፅ ተሀድሶ ልማት ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል ሉባባ ጀማል በበኩላቸው ታራሚዎች በማረሚያ ቤት የእርምት ቆይታቸው ከሚያገኙት አገልግሎቶች መካከል የህክምና አገልግሎት አንዱና መሰረታዊው መሆኑን በማስታወስ በማረሚያ ቤት የሚሰጡ አገልግሎቶች ዘርፈ ብዙ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ማረሚያ ቤቶችን በመደገፍ ታራሚዎችን ለማረም ማነፅ በሚደረገው ስራ ውስጥ ማህበራዊ ሀላፊነታቸውን መወጣት ያስፈልጋል ነው ያሉት።
ያነጋገርናቸው የሲዳማ ክልል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ኮሚሽነር ኮንታሞ ቡርቃ በሰጡት አስተያዬት በክልሉ ባሉ የማረሚያ ተቋማት በእርምት ላይ የሚገኙ የህግ ታራሚዎች ተገቢውን የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ እየተሰራ ነው ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ኢጃራ ጋረደው እና የጋምቤላ ክልል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ኦቦሊ ጣሊያን በሰጡት አስተያዬት ከወርክ ሾፑ መልካም ተሞክሮዎችን እንደወሰዱ ገልፀው ወደተቋማቸው ሲመለሱ ቀደም ብለው ለታራሚዎች ይሰጥ የነበረውን የጤና አገልግሎት ለማሻሻል ከክልላቸው የጤና ቢሮዎች ጋር ተቀራርበው እንደሚሰሩ ነው የገለፁት።
በፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የጠቅላላ ሆስፒታል ስራ አስፈፃሚ ኮማንደር ዶ/ር ተስፋዬ አበራ ታራሚዎች አንድ የማህበረሰብ ክፍል መሆናቸውን በመረዳት በማረሚያ ቤት የእርምት ቆይታቸው ከሚያጋጥማቸው የጤና እክል ቀድሞ መከላከል እንደሚገባና የጤና ሚኒስቴር ለክልል ማረሚያ ቤቶች በግሎባል ፈንድ አማካኝነት ለሚያደርገው ድጋፍ ወቅቱን የጠበቀ የአፈፃፀም ሪፖርት እንዲላክ አሳስበዋል።
በፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የጠቅላላ ሆስፒታል የፕሮጀክቶች ክትትልና ድጋፍ አስተባባሪ ዋና ኢንስፔክተር ሄኖክ አባይነህ በበኩላቸው የማረሚያ ቤቶችን ጤና ሴክተር ለማሳደግ በመረጃ ላይ የተመሰረተ ስራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
አስተባባሪው አክለውም የኤች አይቪ ኤዲስ ስርጭትን ለመግታት የአቻ ለአቻ ስልጠናዎች መስጠትን ጨምሮ ለግንዛቤ ማስጨበጫ የሚያገለግሉ የሚኒ-ሚዲያ መሳሪዎችን እየገዛ ድጋፍ ለሚያደርገው በጤና ሚኒስቴር የኤች አይ ቪ ኤዲስ መከላከልና መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት ምስጋና አቅርበዋል።
በወርክሾፑ ላይ የፌዴራል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን ስትራቴጅክ አመራሮች፣ የሁሉም ክልል የጤና ቢሮ ሀላፊዎችና ባለሙያዎች፣ የICRC ኢትዮጵያ ተወካዮች የሁሉም ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነሮችና የሚመለከታቸው የባለድርሻ አካላት ተወካዮች ተገኝተዋል።
